ውድ የራፋቶኤል ዘኢትዮጵያ ቤተሰቦች እንደምን አላች? ሠላመ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን አሜን።
ውድ የራፋቶኤል ዘኢትዮጵያ ቤተሰቦች ዛሬ ደግሞ ስለ ታላላቅ ብርሃናት ??
‹‹እግዚአብሔርም አለ፦ ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ፤ ለምልክቶች ለዘመኖች ለዕለታት ለዓመታትም ይሁኑ፡፡ በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር ብርሃናት ይሁኑ፤ እንዲሁም ሆነ። እግዚአብሔርም ሁለት ታላላቆች ብርሃናትን አደረገ፤ ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፥ ትንሹም ብርሃን በሌሊት እንዲሰለጥን ከዋክብትንም ደግሞ አደረገ። እግዚአብሔርም በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር አኖራቸው፡፡ በቀንም በሌሊትም እንዲሠለጥኑ፥ ብርሃንንና ጨለማንም እንዲለዩ፡፡ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።›› ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አራተኛ ቀን።›› (ኦሪት ዘፍጥረት ፩፡፲፬-፲፱)
*
ብርሃናት በሰማይ ጠፈር
***
ወሤሞሙ እግዚአብሔር ውስተ ጠፈረ ሰማይ ከመ ያብርሁ ዲበ ምድር፤ አንበሮሙ ሲል ነው፣ በዚህ ዓለም ያበሩ ዘንድ ፈጥሮ ጠፈር በሚባል ሰማይ አኖራቸው
******
አስቀድሞ ቁ.፫ ላይ ብርሃን ይሁን ብሎ ነበር፡፡ እንዴት በድጋሚ ብርሃን ይሁን ይላል? ብርሃን የተፈጠረው ሁለት ጊዜ ነውን? አይደለም ልዩነት አለው፡፡ የመጀመሪያው ብርሃን ቅርጽ አልባ ሆኖ የተገኘ ነበር፡፡ ድብልቅልቅ ብሎ የተሰራጨ ነበር፡፡ አሁን ቅርጽ ያዘ፤ በሚያንጸባርቁ አካላት አማካይነት ተሰበሰበ፡፡ በዚህ መልኩ ባይፈጠር ኖሮ የቀደመው ብርሃን ለሰው ልጆች አጠቃቀም ምቹ መሆን ሳይችል ይቀር ነበር፡፡ እግዚአብሔር የሥርዓት አምላክ ነውና ካለሥርዓት በምስቅልቅል ኹኔታ ውስጥ የነበረውን ብርሃን በአራተኛው ቀን ሥርዓት እንዲይዝ አድርጎ ፈጠረው፡፡
******
እግዚአብሔር ብርሃንን እንደመፍጠሩ የብርሃናት አምላክ የብርሃናት አባት ነው፡፡ አስቀድሞ ብርሃንን ለብቻው ከፈጠረ በኋላ ቀጥሎ ፀሐይና ሌሎቹን የብርሃን አካላት ሠርቶ ብርሃኑን አሳደረባቸው፡፡ እንዲህ መሆኑ ደግሞ ፀሐይን የብርሃናት እናት አድርገው ለሚያስቡ ሰዎች የሐሳባቸውን ስህተትነት የሚያሳይባቸው ነው፡፡
******
በአራተኛው ቀን የተፈጠረችው ፀሐይ ከርሷ በፊት የተገኘውን ብርሃን የምታንጸባርቅ እንጂ ከራሷ የምታመነጭ አይደለችም፡፡ ፀሐይ የራሷ ብርሃን አላት የምትሰኘው ለምድር የምትሰጠውን ብርሃን እንደ ጨረቃ ከሌሎች ከዋክብት የምትቀበለው ባለመሆኑ ነው፡፡
የፀሐይን ተፈጥሮ በፋኖስ ምሳሌነት መገንዘብ ይቻላል፡፡ ፋኖስም እንደ ፀሐይ የብርሃን መሣርያ እንጂ እራሱ ብርሃን አይደለም፡፡ ፋኖስ እሳት አይደለም፤ እሳትን የማንጸባረቅ ችሎታ ግን አለው፡፡ ስለዚህም ብርሃንን ስንፈልግ እሳትን በውስጡ አድርገን ጨለማውን እናስወግድበታለን፡፡
******
በዚህም ፋኖሱ የእሳቱን ብርሃን ለጥቅማችን እንድናውለው የሚረዳን እንጂ እራሱ ብርሃን ወይም የብርሃን ምንጭ እንዳልሆነ ልብ እንላለን፡፡ የአበው ትርጓሜ ስለዚህ ነገር ሲያትት ‹‹በመጀመሪያው ቀን ከፈጠረው ብርሃን የስንዴ ቅንጣት ያህል አምጥቶ ለፀሐይ ቀባት፡፡ ያቺንም ብርሃን ለመላእክት ቢያሳያቸው አስፈራቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ይህችስ ለመላእክት እንኳ ያልተቻለች ለሰውስ አትቻልም፤ ብሎ ከብርሃኗ ከፈለላት›› (አክሲማሮስ ዘቅዱስ ኤጲፋንዮስ)
***
ይህ የፀሐይ ኹኔታ መንፈሳዊ ምሳሌነት አለው፡፡ ሐዋርያው ‹‹በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፤ ስለዚህም በከንቱ እንዳልሮጥሁ በከንቱም እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል›› (ፊልጵ 2፡16) እንዳለው ክርስቲያኖች ከራሳቸው ያልሆነውን ነገር ግን ከእውነተኛው ብርሃን ከክርስቶስ የተቀበሉትን ብርሃን ለዓለም የሚያበሩ መሆናቸውን ይገልጻል፡፡
የብርሃን መመላለሻ የሆነው ፀሐይና ብርሃኑ እንዴት ሊለያዩ ይችላሉ? የሚል ጥያቄ ቢነሳ አምላክ ያንን ማድረግ ይችላል፡፡
ይህንንም ሲያሳየን ሙሴን ለአገልግሎት በጠራው ጊዜ ከሃመልማል ጋር የተዋሐደ ነበልባልን አሳይቶታል፡፡ የነበልባሉ ነጸብራቅ እንዳለ ቢሆንም የማቃጠል ባሕርዩ ግን ከእሳቱ ጋር ስላልነበር ነበልባሉ ሃመልማሉን አላቃጠለም፡፡ ብርሃኑን ከሙቀቱ መነጠል ከቻለ ብርሃኑንስ ከአካሉ መነጠል እንዴት ይሳነዋል? ብርሃናት በእግዚአብሔር ኃይል የሚነጠሉ ወይም የሚቆረጡ መሆናቸውን ክቡር ዳዊት ሲገልጽ ‹‹የእግዚአብሔር ድምፅ የእሳቱን ነበልባል ይቈርጣል›› ብሏል፡፡ (መዝ 29፡7)
* ሁለት ታላላቅ ብርሃናት ??
"ወገብረ እግዚአብሔር ክልኤተ ብርሃናተ ዐበይተ፣ ወኮነ ከማሁ ያለውን ገብረ ብሎ አመጣ፣ እግዚአብሔር ከከዋክብት የሚበልጡ፣ ፀሐይ ጨረቃን ፈጠረ፤ አንድም ደጋጎች ፍጥረታትን ፀሐይ ጨረቃን ፈጠረ፡፡"
***
ፀሐይና ጨረቃ በእይታ ትንሽ መስለው ቢታዩም እንደሚመስሉት ትንሽ አይደሉም፡፡ በግዝፈት ከፀሐይ የሚልቁ ከዋክብት ቢኖሩም ወደ ምድር የሚያደርሱት የብርሃን መጠን ግን አነስተኛ ስለሆነ ፀሐይና ጨረቃ ታላላቅ ተብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ታላላቅ ብርሃናት ቢሆኑም ከፈጣሪያቸው ታላቅነት አንጻር ካየናቸው ኢምንት ናቸው፡፡ የትኛውም ታላቅ ፍጡር ቢሆን የአምላክን ታላቅነት አይገዳደርም፡፡ ስለፍጥረቱ በማወቃችን ውስጥ ስለርሱም እንድናውቅ አድርጎናል፡፡ ስለነዚህ ብርሃናት እንድናውቅ የረዳን አምላካችንን እናመሠግነዋለን፡፡
* ፀሐይ፡
ለምድራችን ታላቅ የብርሃንና የኃይል ምንጭ የሆነው ይህ ታላቅ ብርሃን የመሬትን ብዙ እጥፍ ይተልቃል፡፡ በሰማይ ካሉት ብርሃናት ሁሉ እጅግ ጠቃሚው ነው፡፡ የፈጣሪ እውቀት፣ ጥበብ፣ ኃይል፣ የተገለጠበት በመሆኑም በምድር ላሉ ሁሉ ሕይወታቸው ለመሆን የበቃ ደገኛ ፍጡር ነው፡፡ (መዝ 19፡1-6)
* ጨረቃ፡
ታናሽ ብርሃን ብትሆንም መጽሐፉ ግን ከሁለቱ ታላላቅ ብርሃናት አንዷ መሆኗን ተናግሮላታል፡፡ ምንም እንኳ የተቀበለችውን ብርሃን መልሳ የምታንጸባርቅ ስለሆነች ከከዋክብት ታናሽ ብትሆንም በመሬት ላይ በሌሊት በድምቀት በማብራት የሌሊቱ ገዢ ስለሆነች ከከዋክብቱ የምትበልጥ ነች፡፡
ታላላቆቹን ብርሃናት ታላቅ ያሰኛቸው ግዝፈታቸው ወይም ተፈጥሯቸው አይደለም፤ አገልግሎታቸው እንጂ፡፡ ባላቸው አቅም በትህትናና በልግስና ያገለግላሉ፡፡ "በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን" (ማቴ 20፡26) እንደተባለው ከነርሱ በግዝፈትም ሆነ በብርሃን መጠናቸው የሚልቁ ከዋክብት ቢኖሩም ወደ ምድር የሚያደርሱት ብርሃን ግን በጣም ያነሰ ስለሆነ ሁለቱ ከሌሎቹ ተለይተው ታላላቆች ለመባል በቁ፡፡
** ከዋክብትንም አደረገ፡
ከዋክብት ብዙና የተለያዩ ተፈጥሮዎች አሏቸው፡፡ በዚህ አገባቡ ከዋክብት የሚለው ቃል ፕላኔቶችንና ሌሎች የጠፈር አካላትን በጠቅላላው ያመለክታል፡፡ ሙሴ ዝርዝር ሁኔታውን አልጻፈውም፤ ምክንቱም ዓላማው የእግዚአብሔርን ሥራ መንገር እንጂ ሳይንሳዊ ጥናት ማድረግ አይደለም፡፡ አንባቢውን ወደ ጽድቅ ለመምራት እንጂ ሳይንሳዊ እውቀት ለማስጨበጥ ብሎ አልጻፈም፡፡
*************
** ምሳሌነት፡
በብሔራውያን መተርጕማን እይታ ፀሐይና ጨረቃ እየተለዋወጡ ምሳሌ ሆነው እናገኛለን፡፡ እንደሚከተለው፡- "ፀሐይ የኃጥዓን ምሳሌ፤ ፀሐይ በዋዕዩ ጸንቶ እንዲኖር ኃጥዓንም በኃጢአት ጸንተው ይኖራሉና፤ ጨረቃ የጻድቃን ምሳሌ ነው፤ ጨረቃ ኅጸጽ እንድታደርግ ጻድቃንን ኃጢአት አንድ ጊዜ እሷ ድል ስትነሳቸው አንድ ጊዜ እነሱ ድል ሲነሷት ይኖራሉና፡፡ ‹ስብዐ ይወድቅ ጻድቅ፣ ወስብዐ ይትነሣእ› (ምሳ 24፡16) እንዲል›
አንድም ፀሐይ የጻድቃን ምሳሌ ነው፣ ፀሐይ በብርሃኑ ጸንቶ እንዲኖር ጻድቃንም በምግባር በትሩፋት ጸንተው ይኖራሉና፣ ጨረቃ የኃጥአን ምሳሌ፤ ኅጸጽ እንድታደርግ ኃጥአንም ዕውቀታቸው እያነሰ ይሄዳልና" በተጨማሪም "ፀሐይ የጌታ፣ ጨረቃ የሐዋርያት፣ ከዋክብት የአርድእት ምሳሌ ነው፡፡ አንድም ፀሐይ የባለ መቶ፣ ጨረቃ የባለ ስድሳ፣ ከዋክብት የባለ ሠላሳ ምሳሌ ነው"
ይቆየን!!!
መልካም ዕለተ ሠኑይ
***********************************
ትክክለኛ ቻናሎች እነዚህ ናቸው
• የራፋቶኤል ዘኢትዮጵያ ቻናሎች -
? YouTube channel - Subscribe it now, thanks ❤️
namrud pictures & short films -https://youtube.com/channel/UCCW7MBWOARd2N_xupBoJAxw/videos
? የቴሌግራም ቻናላችን- አሁኑኑ join ያድርጉ
@RAFATOEL ZETHIOPIA
(https://t.me/RAFATOEL_ZETHIOPIA)
?የፌስቡክ ገጻችን- አሁኑኑ Follow/Like ያድርጉ
ራፋቶኤል ዘኢትዮጵያ (https://facebook.com/events/542908322957973/)
?በኢንስታግራም አድራሻችን follow
https://www.instagram.com/Rafatoelzethiopia/
?በድረገጻችን
https://rafatoelzethiopia.websites.co.in
Follow, subscribe እና join ያድርጉ እናመሰግናለን
This site was designed with Websites.co.in - Website Builder
We appreciate you contacting us. Our support will get back in touch with you soon!
Have a great day!
Please note that your query will be processed only if we find it relevant. Rest all requests will be ignored. If you need help with the website, please login to your dashboard and connect to support